Reporter - Amharic Versionኢትዮጵያን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ያገለገሉትና የታሪክ ተማራማሪው ዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ትላንት ታህሣሥ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. በ80 ዓመታቸው ዐረፉ፡፡

ደጃዝማች ዘውዴ በድንገተኛ ሕመም ምክንያት በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ በከፍተኛ ኃላፊነት አገልግለው በርካታ የታሪክ ምርምር ሥራዎችን አበረክተዋል፡፡

ደጃዝማች ዘውዴ የፖለቲካ ጋብቻ ውጤት ተደርገው ሊቆጠሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ አባታቸው ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ ባርያ ጋብርና አያታቸው ራስ ሥዩም መንገሻ በግዛት በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር እስከመዋጋት ደርሰዋል፡፡ ከእርቅ በኋላ ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ በእድሜ በብዙ የሚበልጧቸውን የራስ ሥዩምን ሴት ልጅ ወይዘሮ ወለተ እስራኤልን እንዲያገቡ ተደረገ፡፡ በዚህ ጋብቻ ደጃዝማች ዘውዴ ተወለዱ፡፡ የተወለዱትም አባታቸው በግዞት በነበሩበት በአምቦ ጄልዱ አካባቢ ነበር፡፡

ከአባታቸው ሞት በኋላ እንደገና የደጃዝማችን ማደጊያ ቦታ የፖለቲካ ጋብቻ ውጤት ሆነ፡፡ የራስ ሥዩም ልጅ፣ ደጃዝማች ካሳ በጥፋት ታስረው ከነበሩበት ሊያመልጡ ሲሉ በመገደላቸው በትግራይ መኳንትና በሸዋ ቤተ መንግሥት መካከል ቅሬታውን ለማጥፋት አልጋ ወራሽ አሰፋወሰን ኃይለሥላሴ በሁለት ዓመት የሚበልጧቸውን ልዕልት ወለተ እስራኤልን እንዲያገቡ ተወሰነ፡፡ በዚህ ምክንያት ደጃዝማች ዘውዴ ደሴ አደጉ፡፡

በኢጣሊያ ጦርነት ወቅት እናታቸው በስደት ወደኢየሩሳሌም ይዘዋቸው ቢሄዱም አያታቸው ራስ ሥዩም ለኢጣሊያ አድረው ስለነበረ ወደ አዲስ አበባ ከእናታቸው ጋር ተመለሱ፡፡

ከነፃነት በኋላ ራስ ሥዩም ጣሊያን ትተው ከእንግሊዞች ጋር ሆነው ጄኔራል ዲካዳዎስታን ለመማረክ አምባላጌን በመክበብ ባደረጉት አስተዋፅኦ ንጉሡ በምሕረት ዓይን ስላዩዋቸው ደጃዝማች ዘውዴም ገና በ14 ዓመታቸው የአባታቸውን ግዛት ሽሬን ደጃዝማች ተብለው ለመሾም በቁ፡፡

ደጃዝማች ዘውዴ ሁልጊዜ የራሳቸውን መንገድ የሚከተሉ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ለምሳሌ በከፍተኛ ማዕረግ የተሾሙበትን የሽሬ ግዛት ትተው ኮተቤ ከመጀመሪያዎቹ 43 ተማሪዎች ለመሆን የበቁት በራሳቸው ጥያቄ ነበር፡፡ በራስ የመተማመን ባህሪያቸው ብዙ ጊዜ ታይቷል፡፡ የፍርድ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የፍትህ ሥርዓት እንዲሻሻል ያቀረቡዋቸው አስተያየቶች ስላልተደመጠላቸው ስራቸው ለመልቀቅ ስንብት ጠይቀዋል፡፡ በደርግ ጊዜ ለስብሰባ ከነበሩበት ኒውዮርክ የ60ዎችን መገደል ሲሰሙ ማብራሪያ ጠየቁ፡፡ መልስ ሲከለከሉ አውግዘው ስልጣናቸውን ለቀቁ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ የርሳቸው እምነት ከተማዋ የውሃ፣ የቆሻሻ ማስወገጃዎች ምስረታ ቅድሚያ እንዲሰጠው እንጂ ሕንፃዎች ላይ ማተኮር በጊዜው አስፈላጊ ነው ብለው አያምኑም ነበር፡፡ በዚሁ አቋማቸው የንጉሡን ስሜት ስላሳሰቡ ወደ ሶማሊያ በአምባሳደርነት ተላኩ፡፡

ከ1934 በኋላ ያሉት ዓመታት ለደጃዝማች ዘውዴ የትምርት፣ የአገልግሎት፣ የስደትና የእንደገና መመለስ ጊዜ ናቸው፡፡ ከኮተቤ ትምህርታቸው በኋላ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ባችለር ኦፍ አርትስና ማስተር ኦፍ አርትስ ዲግሪ በፊሎዞፊ፣ በኢኮኖሚክስና በፖለቲካ ሳይንስ አግኝተዋል፡፡ ወደሃገራቸው ተመልሰው የሥራ አገልግሎት ከሰጡም በኋላ እንደገና ወደ እንግሊዝ ተመልስው በታሪክ ምርምር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለማግኘት በቅተዋል፡፡

ደጃዝማች ዘውዴ፣ በባሕር ኃይል የወደብ አስተዳደር፣ የአሣ ልማት ዳይሬክተር፣ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በሱማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በነዚህ ጊዜያት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የአውራ ጎዳና ባለሥልጣናት የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል፡፡

በ1966 አመፅ ሲቀሰቀስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አምባሳደር የነበሩት ደጃዝማች ዘውዴ፣ በልጅ እንዳልካቸው ካቤኔ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው ወደ ሃገር ቤት ተመለሱ፡፡ በደርግ ጊዜም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመስራት ላይ እንዳሉ የ60ዎቹ ባለሥልጣኖች ግድያ ምክንያት ለስብሰባ ከነበሩበት አሜሪካ ተሰደዱ፡፡

ከዚያ በኋላ በተመድ አማካሪነት ከ10 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ ከስደት ወደሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ የጥናት ምርምራቸውን ቀጥለው፣ በአንዳንድ የፖለቲካ ጉዳዮች በሽምግልና በመስራት ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻዎቹ ዕድሜያቸው ለማየት የሚመኙት ምን እንደሆነ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዲህ ብለው ገልፀው ነበር፡፡

“አሁን ምኞቴ ሰላም እንዲፈጠርና የኢትዮጵያ አንድነት እንዲፈጠር ነው፡፡ ሰው መሆን የምንችለው፣ ወደፊት መራመድ የምንችለው አንድነት ሲኖረን ነው፡፡ እርስ በርስ መከፋፈልና መለያየቱ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ድሮ በውጭ ሃገር ያለው ኢትዮጵያዊ ሲለያይ የሚፈቃቀረው፣ አሁን በጎሳ ተለያይቶ ሳይ በጣም አዝናለሁ፡፡ ከመጠን ያለፈ አንድነት በተሻለ መልኩ መጥቶ ሃገራችን ከችግር ከቸነፈር እንድትድን እመኛለሁ . . .”

Advertisements